የፀሐይ ግርዶሹን ያለመመልከቻ መነጽር መመልከት የዐይን ብርሐንን ሊያሳጣ እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ አስጠነቀቀ፡፡


የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኢንስቲዩት እና የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጉዳዩን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የፊታችን እሁድ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ60 እስከ 80 በመቶ ተሸፍና ከፊል ግርዶሽ ይታያል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ያለው ዋናውን ግርዶሽ ግን ከምዕራብ ኢትዮጵያ አንሥቶ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙ ቦታዎች ጎልቶ እንደሚታይ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖልጅ ኢኒስቲዩት አስታውቋል፡፡
በመግለጫው እንደተመላከተው ክስተቱ ከወለጋ አካባቢ ጀምሮ ከፊል ጎጃም እና ከፊል ጎንደርን አልፎ ከዚያም ላል ይበላን አቋርጦ ይሄዳል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ፀሐይ እስክ 99 በመቶ ተሸፍና ቀለበታዊውን ግርዶሽ ማየት እንደሚቻልም ነው የተገለጸው፡፡
ቀለበታዊ ግርዶሽ ማየት ከሚችሉ አነስተኛ ከተሞች (ቦታዎች) መካከል ቡሬ፣ አገው ግምጃ ቤት፣ እንጅባራ፣ ግሽ አባይ፣ ሞጣ፣ ዳሞት፣ ጋይንት፣ ነፋስ መውጫ፣ ጋሸና፣ ሙጃ፣ ዋጃ፣ ቆቦ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ጊራራ እና ላሊበላ ይገኙበታል፡፡
በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ቤጊ፣ ሜቲ፣ መንዲ፣ ጫልቱ፣ በመሳሰሉት ከተሞች ደግሞ ቀለበታዊ ግረዶሽ ባይኖርም ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ ግን እንደሚኖራቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ግርዶሽ ሲፈጠር ክፍተኛ ሃይል ከፀሐይ ሊረጭ ስለሚችል በባዶ ዐይን ማየት ለችግር እንደሚጋልጥ ያመላከተው መግለጫው ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ በማድረግና መነጽር በመጠቀም የታሪኩ አካል መሆን እንዳለበትም አስታውቋል፡፡
ወቅቱ የኮሮና ባይሆን ኖሮ ክስተቱን ለመመልከት ከ20 ሺህ በላይ ጎብኝዎች ተመዝግበው እንደነበር በማመላከትም ይህ ደግሞ በዓለማችን ላይ ውድ ቱሪዝም የሆነው የስፔስ ቱሪዝም አካል ያደርገን እንደነበር ነው ተገለጸው፡፡
ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለዓለም የበለጠ ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡ የግርዶሽ መመልከቻ መነጽር ማግኘት የማይችሉት መስታዎትን ትቁር ጥላሸት በመቀባት የቤት ውስጥ መስኮትና ቀዳዳዎችን በደንብ መሸፈን በሚችል ጥራዝ ሸፍነው ማየት እንዳለባቸውም ተቋማቱ አስጠንቅቀዋል፡፡

Discover more from Mahidere Tsibeb

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
Get started