ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ በ1875ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ።ብፁዕነታቸው ጴጥሮስ የሚለውን ስመ ጵጵስና ከማግኘታቸው በፊት መምህር ኃይለማርያም ይባሉ ነበር።ወላጆቻቸውም በትምህርት እንዲያድጉ ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ወስደው ባህታዊ ተድላ ለተባሉ አባት ሰጧቸው።ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በዚያው አጠናቀቁ።የቅኔ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ወደ ዋሸራ ተሻገሩ፣በዚያም በመምህርነት ተመረቁ።የዜማውንም ትምህርት በሚገባ ለመማር ወደ ጎንደር ተጓዙ። እሱንም እንዳጠናቀቁ ወደ ወሎ ቦሩ ሜዳ በመሄድ ደግሞ ከመምህር አካለወልድ የመጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ብሉያትን፣ ሐዲሳትን እና ሊቃውንትን በብቃት አጠናቀቁ።

በ1900 ዓ.ም በምስካበ ቅዱሳን በመሄድ ወንበር ዘረጉ።በዚያም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔና መጥሐፍትን አስተማሩ።በ1909ዓ.ም ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም በመሔድ ምንኩስናን ተቀበሉ።ሥርዓተ ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ በምሁር ኢየሱስ ገዳም፣በዝዋይ ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት አገልግለዋል። በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ።

ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የራሷን ጳጳሳት ለመሾም ስትነሳ ከተመረጡት አምስት አባቶች መካከል አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ።በዚህም መሠረት ከሌሎች አባቶች ጋር ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተክርስቲያን መዓርገ ጵጵስና ተቀበሉ።ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ።

1928 ፋሽስት ወደኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ በመጀመሪያ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አርበኞቹ ለማበረታታት ተጓዙ። ከዚያም ከተመለሱ በኋላ ወደ ወደ ደብረሊባኖስ በመሄድ የመጣውን ችግር ያሥታግስ ዘንድ እየጸለዩ ለሀገርና ለነጻነት መሞትም ቅዱስ ተግባር መሆኑን በመስበክ ያተጓቸው ነበር።ይሁን እንጂ በሦስት በኩል እየተመራ የመጣው ጦር እል ባለማጥቃቱ ወደየመጣበት ሲመለስ ብፁዕነታቸው ግን “ብችል ጠላት በኢትዮጵያውን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ ካልሆነ እዚሁ እሞታለሁ” ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ። ጠላት በከተማዋ ባሰማራቸው ባንዳዎች ምክንያት እንደልባቸው መንቀሳቀስም አልቻሉም ነበርና እዚሁ ከተማ ተሰውሬ መኖር አልፈልግም ብለው ሐምሌ 22ቀን 1928 ዓ.ም በወቅቱ የኢጣሊያ እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ኃይሉ እጃቸውን ሰጡ።ራስ ኃይሉም ወዲያው ለግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸው።

ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ” ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቆአቸው እርስቸውም የሚክተለውን ተናግረዋል።
“አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ክተቱት። ወዲያው ወታደሮች በሩምታ ተኩስው ገደሉዋቸው። ይህ እንደሆነ አስገድዶ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ።

ማታ ከአስገዳዩ ኮለኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ‘በዚህ ቄስ መገደል አኮ ሕዝቡ ተደሰቷል’ እለኝ እንዴት?’ ብለው ‘አላየህም ሲያጨበጭብ’ አለኝ። እኔም ‘ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጤበጭባል’ አልኩት። ‘እንዴት?’ ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት። እሱም አሳየኝ። ከዚህ በኋላ ” የሆነው ቢሆን እኔእኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቼአለሁ” ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ስዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተስንጥቋል።”ብለው ያዩትን መስክረዋል።

ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የብፁዕነታቸውን አኩሪ ተግባር ትውልድ ሲያዘክርላቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ16 ቀን 1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሐውልት ቆሞላቸዋል።

ሐምሌ16 ቀን 1938 ዓ.ም የቆመላቸው ሀውልት


አቡነ ጴጥሮስ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት ‘ኮርየር ዴላሴራ’ (corriere della sera) የተባለው ጋዜጣ ወኪል እና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ‘ፖጃሌ’ የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓም አዲስ አበባ በነበረ ጊዜ ሂደቱን ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽሑፍ አቅርቦ ነበር:-

“ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ ያለና መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሠየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ‘ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም ዐምፀዋል፣ ሌሎችንም አንዲያምፁ አድርገዋል’ የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም ‘ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊዳኛውም ‘ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ አርስዎ ለምን ዐመፁ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?’ ሲል ጠየቃቸው ፡፡
አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መልስ መለሱ…

“አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ አኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተ ከርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ከርስቲያኔ አቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣረዬ ብቻ የምናገረውን አናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡
ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእከት አስተላለፉ፡፡

”አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡ እንጂ በጎ ለመሥራት፣ እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ።ነጸነታችሁን ከሚረክስ ሙታቹህ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን።”
ጋዜጠኛው ይቀጥላል

“እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣሊያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጎም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሃቀኛ ንግግር አላስተረጎመም፡፡ እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበበ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቢ ተቀምጦ ስለ ነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለ ገለጠልኝ ነው፡፡ እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተስበስቡት ጣሊያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበበ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰማ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር”። ሞት የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሟቸው ስለነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው፣በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው።ብፁዕነታቸው እስከ መቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ ፍጹም ቆራጥነት ይታይባቸው ነበር።”
ምንጭ፡ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን

የሐቀኛው አባታችን በረከት ይደርብን!
ምንጭ:- ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን

Discover more from Mahidere Tsibeb

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
Get started