ነሀሴ 8/2014 ዓ.ም በ ነፃነት ላቀው ከ ባላገሩ ቴሌቪዥን

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፍታ ስንት ነው?
645 ሜትር ፣ ወይስ 145 ሜትር ?
አሁን ላይስ ከፍታው ምን ላይ ደርሷል?
የሶስተኛው ዙር የውሀ ሙሌት ያጠናቀቀው የታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት 22 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ መያዝ ችሏል።
ግድቡ ባለው ከፍታ መያዝ የሚችለው ውሀ የያዘ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በመካከለኛው ክፍል ስድስት መቶ ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል።
ይህም ማለት በአጠቃላይ የሚጠበቀውን 645 ሜትር ከፍታ ለመድረስ 45 ሜትር ገደማ ይቀራል።
በአንፃሩ ደግሞ የግድቡ ከፍታ 145 ሜትር መሆኑም በተደጋጋሚ ይገለፃል።
ከዚህ በመነሳትም 645 እና 145 የሚሉት ቁጥሮች አረዳድ ምንድን ነው ?
የግድቡን ከፍታ ለመግለፅ የሚቀርቡት ሁለቱም አገላለፆች ትክክል ቢሆኑም የተለያዩ መረዳት አላቸው።
በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው የሚገነባው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ነው።
የግድቡ ከፍታ በእርግጥም 145 ሜትር ከሆነ 645 ሜትር ሲባል ምን ማለት ነው?
ግድቡ 645 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል ሲባል ከባህር ወለል በላይ የሚኖረው ጠቅላላ ከፍታ ነው።
ግድቡ እየታነፀ ያለበት የጉባ አከባቢ ከባህር ወለል በላይ 500 ሜትር ከፍታ ያለው ነው።

በዚህ ከፍታ ላይ 145 ሜትር ያለው ግድብ በመገንባት ላይ በመሆኑ የሁለቱ ድምር ግድቡን ከባህር ወለል በላይ እስከ 645 ሜትር ከፍ እንደሚል ልብ ይለዋል።
በአሁኑ ወቅት 600 ሜትር ከፍታ ላይ ነው ሲባልም አሁን ግድቡ 100 ሜትር የሚሆነው ከፍታው ተገንብቷል ማለት ነው። ቀሪውም 45 ሜትር ብቻ ይሆናል።
ባለፈው አመት የተገነባው የግድቡ ክፍል ከፍታ 75 ሜትር ነበር። ወይም የግድቡ ከፍታ 575 ሜትር ነበር ።
በዚህ አመት 25 ሜትር ከፍታ ተጨምሮ 100 ሜትር ከፍታ ላይ ደርሷል። ወይም 600 ሜትር ከፍታ። ይህ የመካከለኛው የግድቡ ክፍል ገፅታ ነው።
በግራ እና በቀኝ ያሉት ደግሞ ከፍታቸው ባለፈው አመት 585 ሜትር ወይም የ85 ሜትር ከፍታ የነበራቸው ሲሆን በተያዘው አመት ከፍታቸው 611 ሜትር ደርሰዋል፤ ወይም 111 ሜትር የሚሆነው ግንባታ ተከናውኗል።
በመጭዎቹ ሁለት ወይም ሁለት አመት ተኩል የቀረው የግድቡ ክፍል ግንባታ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል ።
Leave a comment