
ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው አማሮች ወይም አሞራዊያን ጦረኛ የተራራ ህዝብ ናቸው፡፡ በጥንት ግብጾች ጽሁፍ ቀላ ያሉ፣ ቀለል ያለ ጸጉር ያላቸው፣ ቀጥ ያለ አፍንጫ ያላቸው እና ከርዳዳ-ረዥም ጢም የነበራቸው እንደሆኑ ተመዝግቧል፡፡ ዘፍጥረት 10፡16 ላይ የአሞራዊያን አባት ኤመር የሚባል የከንአን 4ኛ ልጅ እንደሆነም ይናገራል፡፡ ዘኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ላይ ሳባዊያን ከአፍሪካዊያን ጋር እንደተቀላቀሉ፤ በኢትዮጵያ ሳባ ማለት ሰው ማለት እንደሆነ የሚገልጽ ጽሁፍ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ እዚሁ ኢንሳይክሎፔዲያ ላይ ኢዛና በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በግሪክ ድንጋይ ላይ እንደተጻፈው የአክሱማዊያን፣ የሄሞራዊያን፣ የሳቢያን፣ የኢትዮጵያን፣ የሬይዳን እና የስሌ ንጉስ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እዚህ ላይ ሄሞራዊያን የአክሱም ግዛት አካል ነበሩ እያለን ነው፡፡ ሄሞራዊያን ደግሞ አማራ ማለት እንደሆነ አይተናል፡፡ ነገር ግን ኢዛና የትግሬ ንጉስ እንደሆነ አልገለጸም፡፡ ይህ ጽሁፍ በተጻፈበት ዘመን አማራ መኖሩ ሲረጋገጥ፤ ንጉሱም ኢዛና የአማራ ንጉስ እንደሆነ ድንጋይ ላይ ጽፎ አልፏል፡፡ ስለትግሬ ግን የተገኘ ምንም ማስታወሻ የለም፡፡ እናም በዛ ጊዜ ትግሬ የሚባል ነባር ወይም በህዝብነት የሚታወቅ ህጋዊ ነዋሪ ህዝብ ነበረ ለማለት ያስቸግራል ማለት ነው፡፡
ከአክሱም ቀደም ብሎ የነበረው የዳማት ስልጣኔም በብዙ መልኩ አወዛጋቢነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የአማራ አሻራ እንደሆነ መረጃዎችን በማቅረብ መሞገት ይቻላል፡፡ ፊሊፕ ዴቪድ እንደገለጸው ዳማት የሚለው ቃል እስካሁን በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ እንጅ በደቡብ አረቢያ አለመገኘቱ የዚህን አካባቢ ቀደምትነት ያመለክታል፡፡ የሀ ላይ ከተገኙት ጽሁፍ የሰፈረባቸው ድንጋዮች የእጣን ማጨሻዎች ናቸው የተባሉ ቁሳቁስ መገኘታቸውን ይጠቅሳል፡፡ በዳማት ከተጠቀሱት ነገስታት የአንዱ ስም MLK (ምልክ) ሲሆን መለክ ወይም መላክ የሚል ስም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህም በሴማዊያን ቋንቋ ንጉስ ማለት ነው፡፡ ከዚህም ተነስተን ዳማት የጥንት አማራ ስልጣኔ እንደነበር መረዳት እንችላለን፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት በርካታ ጥናቶችን ዋቤ አድርጎ ባጠቃለለው መሰረት ባጠቃላይ ከቀይ ባህር ማዶና ማዶ ስለነበረው ስልጣኔ ምንጭነት አራት የተለያዩ መላምቶች እንደሚሰጡ ያወሳል፡፡ አንደኛው፡ አበሻዎች ወይም ሳባዊያን ከየመን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስልጣኔ አስፋፉ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው፡ ከየመን ሳባዊያን ተሰደው ቢመጡም ባዶ መሬት ሳይሆን በጣም የሰለጠነ ህዝብ ነው ያገኛቸው፣ ተጽእኗቸውም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም የሚል ነው፡፡ ሶስተኛው፡ ሁለቱም ህዝብ አንድ አይነት አየር ንብረት፣ ብዝሀ ህይወት፣ የሰው መልክና ባህል ያለው ህዝብ ስለሆነ የቀይ ባህር ምዕራብና ምስራቅ እንዲሁ በተጓዳኝ እንደ አንድ ወጥ ባህልነትና ስልጣኔነት አደገ የሚል ነው፡፡ አራተኛው፡ ደግሞ ፍልሰት ሲሆን ፍልሰቱ የተከሰተው ብዙዎች እንደሚገምቱት ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን፣ በተቃራኒው ከኢትዮጵያ ወደ የመን ነው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ወደ የመንና አጠቃላይ ደቡብ አረቢያ የተዛመተው ስልጣኔ ምንጩ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ ናት ብለው ይደመድማሉ፡፡
በብዙዎቹ ጥናት የመጨረሻው መላምት የበለጠ ለእውነታው የቀረበ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ተራሮች የስልጣኔ ምንጭ ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ በሌላ ምንጭ እኒህ ዘቢብ አምራች ህዝብ በፑንትም ያንኑ ዘቢብ ማምረታቸውን የሚጠቁም የግብጽ የድንጋይ ላይ ስእል ያሳያል፡፡ ጊዜውም 2480-1155 ዓ.ዓ ነው፡፡ ግብጾች ፑንት ላይ ወርቅ፣ ጥቁር እንጨት፣ ወይራ፣ የዝሆን ጥርስ እና የዱር እንስሳት ይገዙ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በግብጾች አይንም እንደ ገነት ያለ ቦታ ነበር፡፡ ይህም የፑንትና ዳማት ስልጣኔዎች የዛሬው ኢትዮጵያ ስለመሆናቸው ሌላ ማረጋገጫ ነው፡፡ በተለይ ዳማት የተባለው ቃሉ ራሱ ግእዝ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ቃሉ ግእዝ የመሆኑ ነገር ደግሞ በእርግጥም ዳማት የጥንት ግእዝ (አማራ) ስልጣኔ እንደሆነ ደምበኛ ማስተማመኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ሴልደን የተባለ ግሩም ፀኃፊ በግእዝ ድም ማለት መሬት የሚመስል ማለት ሲሆን አዳም ሲሆን ደስ የሚል፣ የሚወደድ፣ ደም ገንቦ፣ ውብ፣ ልከኛ ማለት ነው ይላል፡፡ ስለዚህም አዳም ማለት ከምድር መልክ የተወሰደ ሆኖ የሰው መልክ ማለት ነው፡፡
ከዚህም ተነስተን ዳማት የሚለው የአዳም ወይም የሰው ዘር ቦታ፤ የሰው መገኛ፤ የአዳም አገር ነው ብለን መላምት መሰደር እንችላለን፡፡ ወደ ዚህ መላምት የሚወስደንም በዚህ ፀኃፊ የተገለጠው ነገር ነው፡፡ ሴልደን እንዲህ በማለት ለዚህ አስተሳሰብ ጥንካሬን ያክለበታል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ኢትዮጵያዊያን ለራሳቸው የሰጡት ስም እንጅ ማንም የጫነባቸው አይደለም፤ ለምሳሌ የግሪክ ጸሀፍት በዚህ ስም ጠርተዋቸው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ጠየም ያለ ማለት እንኳ ቢሆን ከሚዲትራኒያን ቢጫማ የሰው ዘር አንጻር ስለሆነ የሚታየው ቀይ ዳማ ማለት ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን መልክ በራሳቸው በኢትዮጵዊያን ቋንቋ አዳማዊ ይሉታል፡፡ የአዳም ትክክለኛ መልክ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ማለት አዳማዊ ማለት ነው፡፡ ይሄም የሰው መልክ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ አብቦ የነበረው የዳማት ስልጣኔም የአዳማዊ ስልጣኔ ነበር ለማለት እንደፍራለን፡፡
ይህም ቀደምት ስልጣኔ ከአማራ ጋር የተያያዘ ወይም በቀጥታ የአማራ እንደሆነ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ በስኮፍ ዋይልፍሬድ ሀርቬይ አርትኦት የተሰጠው በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚታመነው “በኤርትራ ባህር ጉዞ” መጽሃፍ ውስጥ እንደተዘገበው ከአዱሊስ ወደብ የዘጠኝ ቀናት ጉዞ በኋላ ሁሜራይቶች (አማሮች) ይገኛሉ፤ ከእነሱ ጎን ደግሞ ሳባዊያን ይገኛሉ ብሎ ከገለጸ በኋላ በዛ ዘመን ህግ አዋቂው ንጉስ ካሪባኤል የሁለቱ ንጉስ መሆኑን ይናገራል፡፡ እዚህ ላይ መሰመር ያለበት አንድ ነገር አለ፡፡ የአሁኑ ዘመን አማራ እጅግ ሲበዛ ህግ አክባሪ ነው፡፡ ይህም ከጥንት ከአሞራዊያን (ሀሙራቢ ህግ) ወይም የአማራ ህግ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁንም በስኮፍ መጽሃፍ እየተገለጸ ያለው በዚህ በኢትዮጵያ ምድር የሚኖሩት አማሮች ንጉስ ካሪባኤል ህግ አዋቂ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህን እውነታዎች ስናቀጣጥል የጥንት አክሱም፡ የሀ እና ዳማት ስልጣኔ የአማራ መሆኑን እናያለን፡፡ የዛሬው የአማራ ህግ አክባሪነት ለታሪካዊ ሰነዶች ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጠናልና፡፡
ወደ በኤርትራ ባህር ጉዞ መጽሃፍ ስንመለስ አክሱም የጥንት ከተማ ስትሆን የአቢሲኒያ መናገሻ መሆኗ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ነዋሪዎችም ራሳቸውን ኢትዮጵያዊያን ብለው ይጠራሉ፡፡ አቢሲኒያ የሚለው ቃል የመጣው አበሻ ከሚል የአረብ ቃል ሲሆን ትርሙ ድብልቅ የሚል ነው፤ ሄሮዶተስ ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ ጸሀይ ያቃጠለው ፊት ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ ሁለቱም ግን ስህተት ናቸው፡፡ ሀበሻት ወይም ማህራ ይልቅ ለዚህ ስያሜ መጠሪያ ቅርብ ናቸው፡፡ ከቀይ ባህር ወደ ውስጥ ዘልቆ አበሳ ወይም አበሲ የሚባሉ ህዝብ ነበሩ፡፡ በግብጾች ጽሁፍ እንደሚገኘው ግብጽን ከጎበኙ የፑንት ሰዎች ማህራ፣ ሶኮትራ እና ምስራቅ ሶማልያ ይገኙበታል፡፡ በጥቅሉ ሀብቲ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል እጣን ከሚለው የማህራ ቋንቋ የተመሰረተ እንደሆነ የጻፉም አሉ፡፡ ትርጓሜውም እጣን አምራች ማለት ነው፡፡ ሀባሽ (አፋሽ የእኔ አረዳድ) እጣን አምራች (ለቃሚ ማለት ነው)፡፡ እነዚህ እጣን አምራቾች አበሾች ከ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በእጣን ምድራቸው ሁሉ ሀያል እየሆኑ መጡ፡፡ የእነዚህ ሀበሾ ቋንቋም ግእዝ እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ የሀበሾች በኋላ አክሱምን ከተማ አድርጎ ሀያል መሆን ቅድመ-ጊዜ ደቡብ አረቢያ በሚኖሩት ህምያሮችና ሌሎች በጦርነት በመገፋት ነው፡፡ (የኢትዮጵያ ምንጮች ህምያር ማዶ እና ማዶ ሆኖ እንደተዋጋ ይጠቅሳሉ፡፡ ሆሜራይት እና ሳባዊያን አንድ ዘሮች ዮቅጣናዊያን ሲሆኑ ሳባ ቀደምት ነው፡፡ ሴም አርፋክስድን ወለደ፤ አርፋክስድ ሳላህ ወለደ፤ ሳላህ ኤበርን ወለደ፡፡ የኤበር ሁለተኛ ልጅ ዮቅጣን ነው፡፡ ለተጨማሪ፡- የአቶ አጽመ ርስትን እና አለቃ ታየን መጽሃፍት አንብብ፡፡)
በሴልደን ሀተታም ኢትዮጲስ የሚለው የግሪክ ቃል በተለምዶ የተቃጠለ ፊት ማለት ሳይሆን ፈካ/ፈጋ ያለ/ ቀላ ያለ ማለት ነው፡፡ ግሪኮች ከሁለተኛው የአባይ ካታራክት በላይ ያለውን ቦታ ኢትዮጵያ ብለውታል፡፡ እብራይስጦች ደግሞ ይህንን ቦታ ረሽ ኩሽ ማለትም የወርቅ ምድር (ኑብያ) ብለውታል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ኢትዮጵያዊያን ለራሳቸው የሰጡት ስም እንጅ ማንም የጫነባቸው አይደለም፡፡
ግብጾች ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው ፑንት የአማልክት ምድር ነው ብለው ያስቡ ነበር፡፡ ፑንት በግብጾች አጠራር ፓውኔ ይባል ነበር፡፡ ግሪካዊው ኤራቶስቴኒስ በኋላ ይሄንን ቦታ ጣና ላይ የሚገኘው ደቅ ደሴት ነው ብሎ አጣቅሶ ጽፏል፡፡ ጣና በግሪክ ኮሎ ወይ ሴቦ ይባልም ነበር፡፡ ግሪካዊው ታሪክ ፀኃፊና ጅኦግራፈር አርቴሚዶረስ በ2ኛው መቶ ክፍ ዘመን ዓ.ዓ ፑንትን ዳናኪል ነው ካለ በኋላ ሀይቆች እንዳሉት እርሱም አዋሽ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ሆኖም የተረጋገጠ አይደለም፡፡ በሁሴን ሳይድ ሀተታ ደግሞ ፑንት ሱማሌ (ሞቃዲሾ) ናት ያሉ የጥንት አሳሾች አሉ፤ ፑንት አዳል (አውታል፤ አውዳል) ናት ያሉ አሉ፤ አውዳል ማለትም ደሴት ማለት ነው ያሉ አሉ ሲል ያትታል፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ሞቃዲሾ ራሷ አማራ (Xamara) ትባል እንደነበር ሶርያዊው አልሀማዊ በ1220 ዓ.ዓ መጻፉ ነው፡፡
እዚህ ላይ የምንረዳው ሀበሻ ማለት እጣን አምራች ህዝብ (ማህራ ወይም አበሳ ወይም አበሻት ወይም አቢሳን ማለት ሲሆን) ቋንቋውም የዛን ጊዜ ግእዝን ይናገሩ የነበሩት የአማሮች ወይም የኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ በዛ ወቅት አማሮች በእጣን ምርትና ንግድ የታወቁ ነበሩ፡፡ እስከ ኑብያ ያለውን መሬት፣ የዛሬውን የሱማሌና የአፋር መሬት የእጣን ምርት ምቹነት ስንወስድ መረጃው እውነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የበለጠ እውነት የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ በእጣን ምርት አሁንም የአማራ መሬቶች መሪ መሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም ብዙዎች እንደሚሉት አበሻ የአረብኛ ቃል ሳይሆን 1) እጣን አምራች ወይም እጣን አፋሽ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም አበሻ ወይም ሀበሻ ማለት አፋሽ ወይም አምራች ማለት ነው፡፡ 2) ከዚህ ጎን ለጎንም ማህራ ወይም አበሳ የሚል መጠሪያ የነበራቸው እነዚህ ሰዎች አበሻ ለሚለው መጠሪያ በእኩል ደረጃ ተጠሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ 3) ሴልደን በበኩሉ አበሻ (አበሽት) ማለት በሳቢያን ቋንቋ ሪዛሞች ወይም ጺማሞች ማለት ነው ይላል፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች በመነሳት መደምደም የሚቻለው ሀበሻ ማለት አረቦች ለአበሾች የሰጡአቸው ስም ሳይሆን ከእጣን አምራችነታቸው፤ ከሪዛምነታቸው፣ ማህራ (አማራ) እና ከአቢሳ ዘርነታቸው ላይ የተመሰረተ የራሳቸው ለራሳቸው ስያሜ እንደሆነ ነው፡፡ ስለሆነም አበሻ ማለት የሪዛም እጣን አምራች አማሮች መጠሪያ ነው፡፡
የዚህ ታሪክ ባለቤት የሆኑት ሂሚያራይቶች አማራ ስለመሆናቸው እና የመንን፣ ኑብያንና አቢሲኒያን ይገዙ እንደነበር፤ በልብያም የእነሱ ሀያል ግዛት ተመስርቶ እንደነበር ማክሚካኤል የተባለ ተመራማሪ ይገልጻል፡፡ ማክሚካኤል እንደሚያትተው የየመን ገዥ በነበረው የአብርሀ ልጅ አፍሪቃስ (ኢብን አፍሪቃ) አማካኝነት ወደ ልብያ ዘምተው በ46 ዓ.ዓ ሳንጋ እና ከተማ (ያው በቀጥታ ከተማ ማለት ነው) በተባሉ ቦታዎች ለጦርነት ሰፍረዋል፤ በኑቢያም እንዲሁ ወረራ አድርገው ሰፍረዋል፡፡ በዚህ ዘመን ግን በአቢሲኒያም በደቡብ አረቢያም አንድ አይነት የጸሀይ አምልኮት ተንሰራፍቶ ነበር፡፡ የመጨረሻው የሂምያራይት ስርዎ መንግስት መሪ የነበረው አቡ መለክ ወደ ኑብያ ሄዶ ኤመራልድ ፍለጋ በአሸዋ ሰምጦ ቀርቷል፡፡ የዚህ የአሸዋ ውስጥ ሰመጣ ታሪክም በኢትዮጵያ ከሚታወቀው የአክሱም ንጉስ ወደ ግብጽ መንገድ ሲሄድ እስከ ሰራዊቱ በአሸዋ ሰምጦ መቅረት ታሪክ ጋር ይገናኛል፡፡ ይሄንንም ለማረጋገጥ ማክሜካኤል ሂምያራይቶች ቤጃንና ግብጽን መውረራቸውን ያረጋግጣል፡፡ ይሄም በሌላ ምንጮች ኢትዮጵያዊያን ግብጽን ገዝተዋል የሚለውን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ የሂማራቶችን ቁልጭ ያለ የአማራነት ማንነት የሚያስረዳ ነው፡፡ ማክሚካኤል አቢሲኒያዊያን ወይም ሂምያራይቶች በየመን ተመሳሳይ ዝርያ እንዳላቸው እና በቀይ ባህር ዳርቻዎች ላይ የንግድ የበላይነትን እንደተቆናጠጡም ይገልጻል፡፡
በኪያኔ ሀተታም ሰሜን ኢትዮጵያ ትግሬን፣ አማራን፣ ጎጃም፣ ሸዋን እና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን ሂምያራይቶች ማለትም አማሮች በፖለቲካና በባህል የበላይነት የመሩት አገር እንደነበር በማያሻማ ቃል ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ የደቡብ አረቢያና የዚህ የተራራማው ኢትዮጵያ አገር አንድነታቸውንም ይጠቅሳል፡፡ ከምጽዋ 20 ማይል ደቡብ የሚገኘውን አዱሊስ ወደብን በኢትዮጵያና የመን የሚገኙት ሂምያራይቶች ወይም አማሮች በአንድነት መመስረታቸውንም ይጠቅሳል፡፡ የሂምያራይቶች ወይም አማሮች ይዞታም ይሄን ወደብ ይዞ እስከ ሜሮ ድረስ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ቤንት የተባለው ግሪካዊ በአድዋና አካባቢው የሂምያራይቶችን ወይም የአማሮችን ሀውልቶች እና በሂምያራይቲክ ወይም በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፉ የድንጋይ ላይ ጽሁፎችን አይቷል፡፡ የግሪክና ሮም ግዛቶች በመስፋፋት ላይ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ አክሱምና የተቀረው የኢትዮጵያ ተራራማ አገር በሂምያራይቶች ወይም በአማሮች ኃይልና ባህል እድገት እየተመነደገ እንደነበርም አረጋግጧል፡፡
ኪያኔ እንደሚያትተው ግእዝ የሂምያራይቲክ ወይም የአማርኛ ንጹህ መገለጫ ነው፡፡ የጥንት ግእዝ አብዛኛው ባህርያት በየመን ከተገኙ የሂምያራይቶች የድንጋይ ጽሁፎች ጋር አስደናቂ አንድነት አላቸው፡፡ ይሄ የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ዋናው የባህልና የኃይል ምንጭ ሆኖ ላለፉት ሁለት ሽህ አመታት እንደቀጠለ ምንም ክርክር የለውም፡፡ ጀምስ ብሩስ የዚህን ዘር አሻራ ፍለጋ ቀድሞ በ1768 እ.ኤ.አ ወደ የመን ተጉዞ እንደነበርና ከዛም ወደ ዋናው የአሁን ጊዜ ማእከላዊ የአማራ ግዛት ጎንደር በ1770 እ.ኤ.አ እንደመጣ ይጠቅሳል፡፡ ወደዚህም ምድር የአረብ ፍልሰት እንዳልነበርም ይጠቁማል፡፡ ይሄ ፀኃፊ ግን ትግሬዎችንም ሂምያራይቶች እንደሆኑ ጨምሮ ይገልጻል፡፡ ተከዜንና አባይን ተሻግረው ወደህምራ (አምሀራ) ሲቀላቀሉ አማራ እንደሚሆኑም ስህተት የሆነ ነገር አስፍሯል፡፡ መሳሳቱን የሚገልጸውም ይሄንኑን ሀሳቡን በታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በአማራ (ከተከዜ በታች) እና ትግሬ (ከተከዜ በላይ) የተለያዩ ነገዶች የፖለቲካና የባህል የበላይነት ስትመራ ነበር ማለቱን ስናጤን ነው፡፡ አማሮች ከየመን መጡ ብሎ መጻፉም በሌላ ሰነዶች ውድቅ የተደረገ ሀሳብ በመሆኑ ፀኃፊው ስህተት ለመስራቱ ማረጋገጫ ነው፡፡
ጆን ጊለስ የጥንት ግሪክ ታሪክ በተባለው መጽሀፉ አዜብ ወይም ሳባ ከአክሱም ደቡብ የሚገኝ፣ ከሜሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ወይም ግዛታዊ አንድነት የነበረው በሀይማኖትና የውሀ ትራንስፖርት የታወቀ እንደሆነ ይገልጣል፡፡ የግንኙነት መስመሩም ሜሮ፣ አክሱም፣ አሰብ ወይም ሳባ ነበር ይላል፡፡ ሳቢያ የዛሬው የመን ነው ይልና የአረብ እጣን መገኛ ከቀይ ባሀር ማዶ የመን እና አዴል (አፋር) እንደሆነም ይናገራል፡፡ ሳቢያንስ ለመጀመሪያ ጊዜ በኤርትራ ባህር ተንሳፈው ቅኝት እንዳደረጉም ይገልጻል፡፡ ሆሜራይቶች የሳቢያን አንድ ነገድ ክፍል ሲሆኑ በኮከብ ቆጠራና መድሀኒት እንዲሁም በቅኔና ግጥም እጅግ የታወቁ እንደነበሩ መዝግቧል፡፡ ሆሜራይት ማለት በአረብኛ ዘቢብ (ዘምባባ)፣ ፐርፕል ወይም ቀይ/ጠይም ዳማ ማለት ነው ሲልም መልካቸውን የሚወክለውን ስያሜ ይገልጻል፡፡ በቀይ ባህር አቋርጠው ወደ ሜዲቲራኒያን በመጓዝ ታዋቂውን የፌንቄን ስልጣኔ እንደ መሰረቱም ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ ጆን ጊለስ መጽሃፍ ሳባ የመን ነው የሚለው እና ሳባዊያን ከየመን መጡ የሚለው የተለመደው የብዙዎቹ ምሁራን ስህተተኛ አስተሳሰብ በሌላ ተጨባጭ መረጃዎች ውድቅ የተደረገ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡
Leave a comment