ደብረታቦር ተረራ እና ቡሄ

Mahidere Tsibeb

‹‹ፊትህን አሳዬኝ እና ይበቃኛል፡፡››

የጠራ ውሃና የጠራ ዘመን እየጠበቅን ነው፡፡ የክረምቱ ወራት ተጋምሷል፡፡

አበቦች እንቡጥ እያሳዩ ነው፡፡ ፏፏቴዎች ባዘቶ እየመሰሉ ከተራራው ወደረባዳማ ስፍራው ይፈስሳሉ፡፡ እረኞች ችቦ ሰርተው ተናፋቂዋን ቀን ይጠብቃሉ፡፡ እናቶች ለእረኞች የዳቦ ስጦታ አዘጋጅተዋል፡፡ የነሀሴ ሰማይ ከጥቁር ደመና አልፎ በነጭ ደመና ይሸፍን ጀምሯል፡፡ የማርያምን ፆም የሚፆሙ ክርስቲያኖች በረከት ለማግኘት በሱባኤ ተወስነዋል፡፡ ፆመ ፍልሰታ ትባላለች፡፡ በወረሃ ነሐሴ አጋማሽ ክርስቲያኖች የድንግል ማርያምን እርገትና የኢየሱስን ብርሃነ መለኮት መገለጥ እያሰቡ በተመስጦ ያሳልፋሉ፡፡ ወረሃ ነሐሴ ለክርስቲያኖች ብዙ ትርጉም አላት፡፡

በቅዱሱ ተራራ ሚስጥር ተገለጠ፡፡ ለመለኮት መግለጫ፣ ለፈጣሪው መረገጫ፣ ለበረከት ቃል መምጫ ተምርጧል፡፡ እንደዚያ የታደለ ተራራ የለም፡፡ ፈጣሪውን ተሸክሟል፣ በብርሃን ተጎናፅፏልና፤ ከ500 ሜትር በላይ ከፍታ እንዳለው ይነገርለታል ደብረ ታቦር፡፡ በምድረ ርዕስት ሀገረ እስራኤል ይገኛል፡፡ የታቦር ተራራ ከገሊላ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ታላቅ ሥፍራ ነው፡፡ በ325ዓ.ም ቆስጠንጢኒዮስ ሲነግስ እናቱ ንግሥት ኢሌኒ በቅዱሳን ቦታዎች ላይ ቤተክርስቲያንን ማሰራት በጀመረች ጊዜ በዚህ ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን አሰርታበት ነበር፡፡

ይህም ቤትክርስቲያን በ614ዓ.ም በፈሪሳውያን ፈረሰ፡፡ ሲሰራ እየፈረሰባት ዘመን ዘመን እየተሸጋገረ በአሁኑ ሰዓት በካቶሊኮች የተሰራ ቤተክርስቲያን እንዳለ ይነገራል፡፡ ቅዱስ ነው ከፍ ያለም ነው፡፡ በዚያ ቅዱስ ተራራ ላይ መለኮት በራ፡፡ ጨለማው በብርሃን ተለወጠ፤ እረኞች ቤታቸውን ረሱ፡፡ ቀን እና ሌሊት አልለይ አሉ፡፡ ድምፅ ከሰማይ መጣ፡፡ ምሳሌው ተተገበረ፡፡ ትንቢቱ ተፈፀመ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት መካከል አንደኛው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ በዚያ ታላቅ ተራራ መለኮት የተገለጠበት፣ ክርስቶስ የነብያትና የፍጥረታት ሁሉ ጌታ መሆኑ የታወቀበት ቀን ነው፡፡ በዓሉን ቅዱስ ጴጥሮስ‹‹ የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ›› እንዳለ፡፡

‹‹ ሙሴ ከመቃበር ኤሊያስ ከሰማይ፤ ከጌታ ጋር ዋሉ በደብረ ታቦር ላይ፡ ዳሱስ መልካም ነበር ታስቦ ቢሰራ ብዙ ላይቀመጥ የሰማይ ሙሽራ፡፡ ሙሴና ኤሊያስ ገዳምን ሲመኙ ሚስጥር ጎትቷቸው በደብር ተገኙ፡፡››
ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያቆብን ወንድሙንም ዮሀንስን ይዞ ወደ ረጅሙ ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው፡፡ በፊተቻውም ተለወጠ፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፡፡ ልብሱም እንደብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤሊያስ ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚሕ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡

ብትወድስ በዚህ ሶስት ዳስ አንዱን ለአንተ፣ አንዱንም ለሙሴ፤ አንዱንም ለኤሊያስ እንስራ አለ፡፡ እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ ከደመናው ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ እርሱ ነው፡፡ እርሱን ስሙት›› የሚል ድምፅ መጣ፡፡ ደቀመዛሙርቱም እርሱን ሰምተው በፍርሃት ወደቁ፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዳሰሳቸውና ተነሱ አትፍሩም አላቸው፡፡ አይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ በቀር ማንም አላዩም፡፡

ከተራራው በወረዱ ጊዜ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሳ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው፡፡ ይህን ያለበት አንድም ውዳሴ ከንቱ ስለሆነ፣ ሁለትም የሚያምኑበት ጊዜ ገና ስለሆነ፣ መከራን ወደኋላ አስቀምጦ ክብርን መናገር ስለማይገባ፣ ሰውን ሁሉ እየሰበሰበ ታምር እያሳየ እያሉ እንዳያውኩና ምክንያት እንዳያገኙ ለማድረግ ነው ይላሉ አበው፡፡

ክብሩን እና መለኮቱን የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢገልጥ ፍጡራን የማይችሉት ጌታ ምሳሌውንና ትንቢቱን ለመፈፀም ወደዚህ ተራራ ወጣ፡፡ በዚሕ ተራራ ባርቅ ሲሳራን ከነሰራዊቱ ድል አድርጎበታል፡፡ ይህም ባርቅ የጌታ ምሳሌ ሲሆን ሲሳራ ደግሞ የአጋንት ምሳሌ ነው ይላሉ አበው ፡፡ ጌታ በደብረታቦር ክብሩን በመግለጥ አጋንትን ድል የሚነሳ ስለሆነና ስለነሳ ነው፡፡ ትንቢቱ ደግሞ ዳዊት በመዝሙሩ ታቦርና አርሞኒዬም በስምህ ደስ ይላቸዋል እንዳለ ያን ትንቢት ይፈጽም ዘንድ በደብረታቦር ተገለጠ፡፡

ኢየሱስ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዬው ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አሉ እንዳለ ዘመነ ምፅዓት እስኪመጣ ድረስ ሞት የማይነካቸው ሰዎች እንዳሉም ያሳይ ዘንድ ወዷልና፡፡ ኢየሱስ እሞታለሁ ቢል ቅዱስ ጴጥሮስ አይደረግብህ ብሎት ስለነበር የባሕሪ አባቱ አብን እርሱን ስሙት ለማስባልም ወደዚህ ተራራ ወጣ ይላሉ አበው፡፡
በባሪያው በቅዱስ ጴጥሮስ አንደበት አንተ ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ ነሕ ተብሎ የተነገረውን ዳግመኛ በአብ ለማስመስከር፤ በቄሳሪያ ከነብያት አንዱ ብለውት ነበርና ነብያትን ጠርቶ የነብያት ጌታ እንደሆነ ለማስመስከር ነው፡፡

ኢየሱስ ወደ ደብረታቦር ተራራ ሶስቱን ብቻ ለምን ይዞ ወጣ? ጴጥሮስን ያቆምብና የያቆብን ወንድም ዮሀንስን ብቻ ነው ይዞ የወጣው፡፡ ቅዱስ ዮሀንስ እና ቅዱስ ያቆብ በጌታ ቀኝና ግራ ለመቆም እናታቸውን አስለምነውታል፡፡ ያስለመኑትም ለጊዜው ሹመት ሽልማት ሽተው ነው፡፡ ለፍጻሜው ግን ለፍቅሩ ሳስተው ነው፡፡ እኔ ልጠጣው ያለውን ፅዋ መጠጣት ትችላላችሁን ባላቸው ጊዜ አዎን እንችላለን ማለታቸው ለፍቅሩ ሳስተው በመንደዳቸው ነበር፡፡ ይህን ፍቅራቸውን በማዬትም ሶስቱን ወደተራራው ይዟቸው ወጥቷል፡፡ እነዚህ ባለሟሎቹም ናቸው፡፡ የሚስጥር ደቀ መዛሙርቱም ናቸው፡፡

ኢየሱስ ወደተራራው ሶስቱን ይዞ ሲወጣ ስምንቱን በተራራው ግርጌ ትቷቸው ሄደ፡፡ ይህም በይሁዳ ምክንያት ነው ይላሉ አበው፡፡ ይሁን እንጂ በእርሰ ደብር የተገለፀው ሚስጥር በእግረ ደብር ለነበሩት ለስምንቱም ተገልጿል፡፡ ደብረታቦር የወንጌል ምሳሌ ናት ይባላል፡፡ ለምን ካሉ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፡፡ ከቁንጮው ከወጡ በኋላ ግን ሜዳውንም ሸለቆውንም ያሳያል፡፡ ወንጌልም ሲማሩት ያስቸግራል፡፡በብዙ ድካም ከተሟሩት በኋላ ግን ጽድቅን ከኩነኔ ለይቶ ያሳያል፡፡ ይህ ተራራ በመንገስተ ሰማያትም ይመሰላል፡፡ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናትም ይሏታል፡፡

የሙሴና የኤሊያስ በዚህ ተራራ ላይ ለምን ተገለጡ? ሙሴ ከመቃበር ኤሊያስ ከብሔረ ሔዋን ነበር የመጡት፡፡ ሙሴ 570 ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ተነጋግሯል ይላሉ አበው ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን የአምላኩን ፊት ማዬት አልቻለም፡፡ እርሱም ‹‹ፊትህን አሳዬኝና ይበቃኛል›› ብሎ አምላኩን ተማፅኖ ነበር ፡፡ ፊት ለፊት ተገለጠልኝና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኜቴን ልወቀው አለ፡፡ ጌታ ግን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አታይም ፡፡ ሰው ሆኜ እስክገለጥልህ ድረስ አንተም በመቃበር ተወስነህ ትኖራለህ አለው፡፡ ያንም ቃል ለመፈፀም ነበር ሙሴን ከመቃበር አስነስቶ በደብረታቦር ላይ ያቆመው፡፡ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል? ብሎ ጠዬቀ፡፡ አንዳንዶች አንተ ዮሃንስ ነህ፡፡ ቀሪዎች ኤሊያስ ነሕ፡፡ ኤሪሚያስ ነህም ይሉኃል አሉ፡፡ ከነብያት አለቃ አንዱ ነው ይሉሃል አሉ፡፡ ሰዎችስ እንደዚህ አሉ እናንተስ ምን ትለላችሁ ? አለ፡፡

ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ አለው፡፡ ሙሴ የመጣበት ምክንያት አንድም በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን የጥርጣሬ መንፈስ ለማስወገድ ነበር፡፡ ነብዩ ኤሊያስን ደግሞ አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ ብሎት ነበርና ይህን ለማድረግ አመጣው፡፡ በደብረታቦርም ኤሊያስ አንተ የኤሊያስ ጌታ እንጂ አንተ ኤሊያስ አይደለህም፡፡ አንተ የሙሴ ጌታ እንጂ ሙሴ አይደለህም፡፡ በማለት መሰከሩ፡፡ በዚህ ቀን ኢየሱስ ጌታ እንጂ ሙሴም፣ ኤሊያስም፣ ከነብያትና ከሃዋርያት ወገን እንዳልሆነ ተረጋገጠ፡፡

አበው በዚያ ቅዱስ ተራራ መልስ ተመልሷል፤ ጥርጣሬ ተወግዷል ይላሉ፡፡ ለምን ካሉ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን ገልጦ አምላክ መሆኑን አሳይቷልና፡፡ ጌታ ትንቢቱን ለመፈፀም ደብረታቦርን ለምን መረጠ? ‹‹ታቦርና አርሞኒዬም በስምሕ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፡፡ ስምህን ያመሰግናሉ፡፡ ›› እንዳለ ይህን ትንቢት ለመፈጸም ሲል በደብረታቦር ሚስጥሩን ገለፀ፡፡ ይህ በዓል በምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ› ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለ ኾነ በዓሉ ‹ቡሄ› ተብሎ ይጠራል፡፡

በዓለ ደብረ ታቦር ጌታ ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት ዕለት ስለሆነ ‹የብርሃን› በዓልም ይባላል፡፡በዓለ ደብረታቦር እረኞች ብርሃኑንና ግርማውን አይተው ተደሰቱ፡፡ ወደቤታቸው መሄዳቸውንም ረሱት፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸው ስለቀረባቸው ለመንገድ መጥረጊያ ችቦ እያበሩ ለረሃባቸው ደግሞ ሙልሙል ይዘው ሔዱ፡፡ ይህን ለመዘከር ዛሬም ይደረጋል፡፡
ደብረታቦር ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫(13) ቀን ይከበራል፡፡ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም ተብሎም ይታመናል፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› ይላሉ፡፡

በቡሄ ችቦ ይበራል፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ እረኞች ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ ይሰነብታሉ፡፡ ‹‹ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ ሙልሙል ወይም የቡሔ ዳቦ ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ሙልሙል እየበሉ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት ምሳሌ ሲኾን፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡም ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡

ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ እንዳለ ተዘጋጅቶ መጠበቅ መልካም ነው፡፡ ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይፈጥናል እንዳለ ዘመኑ ይቸኩላል፡፡ ይፈጥናል፡፡ በሚሮጥ ዘመን ውስጥ ታገኝ ዘንድ ሩጥ፡፡ ሮጦ ለማግኜት ፈጣሪን ያዙ ይላል፡፡ በልባችሁ መለወጥ ታደሱ እንዳለ መለወጥ በልባችሁ ይሁን፡፡ ለመላው የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ እንኳን ለበዓለ ደብረታቦር በሰላም አደረሳችሁ፡፡

መልካም በዓል ተመኘንላችሁ ማህደረ ጥበብ

ምንጭ:- አብመድ

ማህደረ ጥበብን በተለያዩ አማራጮች መከታተል ይችላሉ 👇👇👇👇👇👇👇👇👇

Discover more from Mahidere Tsibeb

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
Get started