
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን የእዳ ደብዳቤ ይቀድ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን በደሙ ያጸና ዘንድ በእለተ አርብ የደረሰበትን መንገላታት በአጭሩ ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍን ገለጥ አድርገን እንመልከት ፡- (ማቴ. 27÷27-31)
👉 ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ለሊቱን ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ በኾነው በይሁዳ መሪነት ታግዘው ከያዙት በኃላ እያንገላቱት ወደ ሐና ወሰዱት፡፡
👉 ሐና ከፊት እየመራ እየደበደቡ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ቀጥሎም ወደ ጲላጦስ ወሰዱት፡፡
👉 ከጲላጦስ ወደ ወደ ሔሮድስ በማመላለስ እንዲንገላታ ተደርጓል፡፡
👉 በሂደቱም እየሰደቡትና እየዛቱበት ፊቱን በጥፊ ራሱን ደግሞ በዱላ ይመቱ አሰቃይተውታል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰውልጆች ነጻ መውጣት ሲል በዕለተ ዓርብ ከሦስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት የተቀበላቸው መከራዎች በጥቂቱ ስንቃኝ፡-
👉 በጅራፍ ተገርፎአል፡፡
👉 መስቀሉን ተሸክሞ በቀራንዮ ተራራ እየወደቀ እየተነሣ ተጉዟል፡፡
👉 የገዢው የጲላጦስ ወታደሮችም እያዳፉት፣ ርኩስ ምራቃቸውንም እየተፉበትና እያፌዙበት ወደ ተራራው እንዲወጣ ተደርጎአል፡፡
👉 የነቢያት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ልብሱን ገፈው ከለሜዳ አልበሰውታል፡፡
👉 በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጥለው ተካፍለውታል፡፡
👉 የእሾህ አክሊል ጉንጉን በራሱ ላይ በማድረግ የሰማይና የምድር ንጉሥ እያሉ ተሳልቀዋል፡፡
👉 ጎኑን በጦር ወግተውታል፡፡
👉 እጆቹን እና እግሮቹን በ5 ችንካሮች ቸንክረው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል፡፡
በመስቀል ላይ እያለ ከተናገራቸው ውስጥ፡-
👉 እየበደሉት እሱ ግን ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው›› ይል ነበር፡፡
👉 ‹‹እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ››
የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በክርስቶስ ላይ ያቀረቡት መሠረተ ቢስ ክስና ውንጀላ፡-
👉 ለቄሳር ግብር መክፈል አይገባም በማለት አስተምሮል፡፡
👉 ዕለተ ሰንበትን ሽሮአል፡፡
👉 ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏል የሚሉ ናቸው፡፡
የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በክርስቶስ ላይ ያቀረቡትን መሠረተ ቢስ ክስና ውንጀላ ለማጽናት የሄዱበት እርቀት፡-
👉 በሐሰት የሚመሰክሩ ምስክሮችን በገንዘብ አባብለውና አደራጅተው አስመሰከሩ፡
👉 በርባን የተባለው ወንጀለኛ እንዲፈታ ንጹኸ ባሕሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንዲሰቅለው ገዥው ጲላጦስ ልመና አቅርበዋል፡፡
👉 የገዥው ጲላጦስ ባለቤት በሕልም ተረድታ እጁን በጻድቅና ንጹሕ ሰው ደም እንዳያስገባ ስለመከረችው ‹‹እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› በማለት እጁን ከታጠበ በኋላ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡
👉 ገዥው ጲላጦስ ንጹህ መኾኑን እያወቀ ወንበሩን ለማጽናት በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሰጠው የተዛባ ፍርድ ለትምህርት ይኾን ዘንድ ሲታወስ ይኖራል፡፡
👉 የኢየሱስ የስቅለት ውጣ ውረድ ለእውነት መቆምን፣ ከተዛባ ፍርድ መቆጠብን፣ ከሐሰት ምስክርነት ራሰን መጠበቅን፣ እስከመጨረሻው መጽናትን፣ ምልጃን፣ እስከሞት የሚያደርስ ፍቅርን እንማርበት ዘንድ እነኾ አብነት ኾኖ ዛሬም ዘልቋል፡፡
Leave a comment