የሰፋ ሀገር ይዘን፣ ጠቦ መሞት ይብቃን (ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ)

“…የሰፋ ሀገር ይዘን፣ ጠቦ መሞት ይብቃን፤…”(ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ)

ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ

ጠላቴነው ብለህ ባልበዘበዘበት አስረህ ከምታሸው፣
ግዴለህም ጎበዝ እስኪ መጀመሪያ ፈታሹን ፈትሸው፣
የሸንጎ ጠብ ጠና ዳኛ ባከረረው ፣
ሀገር ይጫረሳል ገላጋይ በጫረው፣
ገዳዪም ዋይ ዋይ ነው የሞተበትም ዋይ፣
እንዴት እንሰረው መቃብሯን ታቅፎ የሀገሬን ገዳይ።
አይችለው የለ እንጂ – የልባም ትከሻ፣
ከውርደቱ ደጃፍ – ነውሩን ማምለጥ ሲሻ፣
ገርፎ ማሳመን ነው፣ የፈሪ ሰው በትር፣ የሽንታም ሰው ጋሻ።
እንመን ግድ የለም…
ፍትሕ አይታለምም – ሐቁን እየሸሹ፣
የጠፋው እንዲገኝ፣ እስኪ መጀመርያ፣ ይፈተሽ ፈታሹ፤
አቀርቅራ ታዝግም፣ ትጎናበስ እንጂ፣ መሔድ እስኪያድላት፣
ሰብረህ ስታበቃ፣ ‘ምርኩዝ እንቺ’ ብለህ ደርሰህ አትደልላት፤
‘በኔ ብቻ’ በሽታ – ጥበት እየቀጣን፣
በ’ናታችን ርስት፣ ባባታችን መሬት፣ መደገፊያ እያጣን፤
ቁልቁል እያሰቡ – ምንድነው ከፍታ፣
መብት እየነጠቁ – ምንድነው ግዴታ?
እስከ መቼ ተረት – ምንድን ነው ይነጋል፣
መንገድ እየቀሙ – ምርኩዝ ምን ያደርጋል?
አንተ እንደሁ ልማድህ አለስልሶ መግደል አሳስቆ መግፋት፣
‘ካብኩ’ እያሉ ‘ማቅለል’ ‘ሳምኩ’ እያሉ ‘መትፋት’፣
የበደል ላይ ጀግና – ሬሳ ላይ መዛት፣
መዋረድን ሽሽት – የአሽቃባጭ አፍ መግዛት፤
እየሸሹ ትግል – እየሮጡ ዛቻ፣
በጉንዳን ልቡና – የነብር ዘመቻ፤
የበላ እያሠረ – የቀማ ቢገፈው፣
የሳተ እያረመ – ያጠፋ ቢገርፈው፤
ጀግና ልማዱ ነው፣ ባርያ ሆኖ ታሽቶ፣ ንጉሥ ኾኖ መግዛት፣
እያነሰ ገዝፎ – እየሞተ መብዛት፤
ያ ሽንታም ላመሉ – በሬሳ ይፎክራል፣
ከፈሪ ገዳይ ‘ድል’ – የጀግና ‘ሞት’ ያምራል፤
ይልቅ……
በእኔ ልቅደም ትርክት- የዘር ደዌ አያጥቃን፣
ከጎጥ ቀንበር ፍቱን – ጠቦ መሞት በቃን፤
የጸደይ ወይን ኾኖ – የሐቅ እንባ ቢጥም፣
በድሎ መጀገን – ጀብድ ሆኖ ቢረግጥም፣
የትግላችን ልኩ – ያሳር ደም ቢያስምጥም፣
በሰፋ ሀገር ጠበን – ኢትዮጵያን አንሰጥም!!!

Discover more from Mahidere Tsibeb

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
Get started