ሚስት እንዴት መምረጥ እንችላለን

ማህደረ ጥበብ

በትዳር አጋር መማረርን ልማድ ከማድረግ በቂ ጊዜ ወስደን ማሰብና መግባት ያሻል። አፈ በረከት ጥዑመ ልሣን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማግባት ለሚሹ ሰዎች ሁለት አማራጮችን አይተው እንዲገቡ ይመክራል።
➊. የፈለጋትን ሴት አግብቶ ሁሉንም ታግሶ መኖር
➋. ከገቡ የማይወጡበት ሕይወት ስለሆነ በጥንቃቄ መርምሮ በማስተዋል ማግባት።
እንዲህ ይለናል:- (በአንድ ጾታ የተጻፈው ለሁለቱም ጾታ እንደሆነ ይታወቅ)
«….በዚህም የሚስቶቻችሁን ጥፋቶች በሙሉ በጽናት ለመቀበል ውሳኔአችሁን ጥብቅ አድርጉት። ይኽ ከባድና ልትሸከሙት የማትችሉት ነገር ከሆነባችሁ መልካም፣ ደግና ታዛዥ ሚስት ለማግባት ማንኛውንም አይነት ጥንቃቄ አድርጉ። ከእነዚህ ከሁለቱ ምርጫዎች አንደኛውን ልትመርጡ ግድ እንዳለባችሁ እናንተም ታውቃላችሁ። መጥፎይቱን ሚስት የምትወስዱ ከሆናችሁ ብስጭቱን በጽናት ልትሸከሙ ግድ አለባችሁ። ይኽን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆናችሁ። እርሷን በመፍታት የዝሙት ወንጀልን (ኃጢአትን) በራሳችሁ ላይ ታመጣላችሁ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል።»
_ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል። የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” (ማቴ ፭ : ፴፪ ማቴ ፲፱ : ፱) እነዚህን ሕግጋት የምንመረምራቸው ከሆነና ከጋብቻ በፊት በሚገባ ያወቅናቸው ከሆንን ሚስት ለመምረጥ ታላቅ የሆነውን ጥንቃቄ እናደርጋለን። ይኽችም ሚስት ገና ከመጀመሪያው ጊዜ አንሥቶ በሚገባ የምትታዘዝና ከእኛ ጠባይአት ጋር የሚስማሙ ጠባያት ያላት ትሆናለች። እንዲህ ያለችውን ሚስት የምናገባ ከሆነ እኛ ልናገኘው የምንችለው ጥቅም እርሷን ፈጽሞ አለመፍታት ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳዘዘን በጥልቀት እንወዳታለን። እርሱ:- “ባሎች ሆይ:- ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” (ኤፌ ፭ : ፳፭) ብሏል። ቅዱስ ጳውሎስ የፍቅርን ልኬታ ሲሰጠን “ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት” ብሎ ነገረን። ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን የወደዳት እንዴት ነው? ንገሩኛ! እርሱ ለእርሷ ራሱን ነው የሰጣት። ስለሆነም ስለሚስትህ መሞት የሚገባህ ከሆነ ልትሞትላት ግድ ነውና ይኽን አላደርግም አትበል። እግዚአብሔር አምላክ አገልጋይ ባሪያውን አጥብቆ ከወደደና ራሱን ለእርሷ አሳልፎ ከሰጠ አንተ ደግሞ ከዚህ አስበልጠህ አጠገብህ ያለው ባልንጀራ አገልጋይህን ልትወደው ግድ ነው።
በሰውነታችን ላይ ቁስል ቢወጣ እጆቻችንና እግሮቻችንን ቆርጠን አንጥልም። የደረሱብንን በሽታዎች እናጠፋለን እንጂ። ለምሳሌ:- በቆሮንቶስ የነበረውና የአባቱን ሚስት አግብቶ የነበረው ሰው የቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። ጌታ እግዚአብሔር ግን ከአባልነት አልቆረጠውም። ፈወሰው እንጂ። (፩ኛ ቆሮ ፭ : ፩) ለሚስትም ልናደርገው የሚገባን ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ግድ ነው። በእርሷ ውስጥ አንዳንድ ጥፋቶች ቢኖሩም ሚስትህን አትተዋት። ክፉውን ከእርሷ ዘንድ አስወጣ እንጂ። “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” ተብሎ ስለተጻፈ (ዘፍ ፪:፳፬ ማቴ ፲፱:፭ ኤፌ ፭:፴፩) እርሷም የአንተ እጅና እግርህ ናት።» በማለት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ ይነግረናል።
የትዳር ሕይወት በመከባበር፣ በመቻቻልና በትሕትና የሚኖሩት የተግባር ኑሮ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ የጻፈልንን ስንመለከት “ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው።” (ቆላ ፫:፲፰-፲፱) በማለት ይነግረናል። እስከመጨረሻው ተከባብሮ ቢኖሩ ውጤቱ ጣፋጭ ነው። በሥጋ ባንጠቀም እንኳ በነፍስ እጅግ ተጠቃሚ ነን።


በ17ኛው መክዘ ከተነሡት እንስት ኢትዮጵያውያን ቅዱሳት መካከል አንዷ የሆነችው ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ከንጉሥ ሱስንዮስ ጋር ተጋጭታ ወደ ዋልድባ ገብታ ነበር። እዚያ እርስዋ በገባችበት የሴቶች ገዳም ውስጥ የነበረች አንዲት አሮጊት ነበረች። ይህች ሴት ጠባይዋ እጅግ አስቸጋሪ ነበር ይባላል። ምንም ዓይነት በጎ ነገር ቢደረግላት ትራገማለች እንጂ አታመሰግንም። የሚያገለግሏትንም ሁሉ ትነዛነዛለች። አንዳንዴም ትማታለች
ወለተ ጴጥሮስ ምክንያቱን ስትጠይቅ የሴትዮዋን የጠባይ ክፋት ነገሯት። እርስዋም ይህንን ስትሰማ ‹እኔ አገለግላታለሁ› ብላ ወደ ሴትዮዋ ሄደች። እጅግ የንትወዳትና የምታከብራት ጓደኛዋ እኅተ ክርስቶስ እንኳን በውሳኔዋ ተገርማ ሐሳቧን እንድትለውጥ ስትነግራት ፈቃደኛ አልሆነችም ነበር። ለሴትዮዋ ትታዘዛለች፣ ምግብ ታበስላለች፣ ቤቷን ትጠርጋለች፣ ሰውነቷን ታጥባለች፣ ትላላካታለች፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስዳታለች። ይህንን ሁሉ ብታደርግላትም ግን ሴትዮዋ አትደሰትም ነበር። ይልቁንም ታማርራለች፤ ትራገማለች፤ ትሳደባለች፤ ትተቻለች፤ ታንቋሽሻለች፤ ከዚያ የባሰም ሲመጣ ትማታለች። አንድ ቀን እንዲያውም ወለተ ጴጥሮስ ለእርስዋ ምግብ እየሠራች እያለ ከምድጃው እሳት የያዘ እንጨት አውጥታ በፍሙ መትታት ነበር። ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ግን አንዲትም ቀን አማርራ አታውቅም ነበር። ነገሩንም ሁሉ በምስጋና ትቀበለው ነበር እንጂ። ይህ ነገርዋም ስትሰድባትና ስታማርራት ለሚሰሙት ሌሎች እኅቶች ግራ ይገባቸው ነበር። “ለምን አትተያትም? ምን ትጠቅምሻለች? እንዲህ ከምትረግምሽ ሴት ምን በረከት ይገኛል” ይሏት ነበር። እርስዋ ግን መልስ ሰጥታቸው አታውቅም። ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገለቻት በኋላ ሴትዮዋ ሞተች። ወለተ ጴጥሮስም እጅግ አዝና እና አልቅሳ ቀበረቻት። የደረሰባትን ሁሉ የሚያውቁት እኅቶችም እንደዚያ በማልቀስዋ ተገረሙ። አንድ ቀንም እንዲህ ብለው ጠየቁዋት ‹‹ለመሆኑ ምን አድርጋልሽ ነው አብረሻት የኖርሽው? ከእርስዋስ ምን አገኘሽ? ደግሞስ ምን ጎድሎብሽ ነው በመሞቷ ያለቀስሽው?» ወለተ ጴጥሮስም እንዲህ አለቻቸው።
«ንብ ታውቃላችሁ? ንብ መልከ ጥፉና ክፉ ናት። መርዟም ሰው ከነደፈ ይጎዳል ያማል። አንዳንዴም ለመሞት ያደርሳል። ማንም የንብን ጠባይ አይወደውም። ከንብ ይልቅ ዝንብ ጠባይዋ መልካም ነው። አትናደፍም፤ መርዝ የላትም፤ አትጎዳም፤ በመርዟም ለሞት አታደርስም። ዝንብን የንብ ያህል ማንም አይፈራትም። ዝንብ ግን ማር አትሠራም። ለዝንብ ማንም ቀፎ አይሠራላትም። ምክንያቱም ማር የላትም። ሰው ሁሉ የንብን ጠባይ ታግሦ፣ መርዟንም ተከላክሎ ለማርዋ ሲል አብሯት ይኖራል። ማንም ስለ ንብ ክፋትን መርዝ አያስብም፤ ስለ ማርዋ ነው እንጂ። እኔም እንደዚያው ነው፡፡ ይህች ባልቴት ጠባይዋ ክፉ ነው፡፡ ነገር ግን ከእርስዋ ዘንድ እንደ ማር የሚገኝ ብዙ በረከት አለ። ንብ ሌላውን የምትጠቅመውን ያህል ለራስዋ አትጠቀምም፤ ይህችም ሴት እኔን የጠቀመችኝን ያህል ራስዋን አልጠቀመችም። እዚያ ቤት ብዙ ነገር አግኝቻለሁ። ጠባይዋን ታግሼ፣ መርዝዋንም ተከላክዬ ብዙ ማር ቆርጫለሁ። እናንተ መናደፏንና መርዟን ብቻ ነው የምታዩት። ማርዋ ሊታያችሁ አልቻለም። እኔ ደግሞ ማሩ እንጂ መናደፏ አልታየኝም።» አለቻቸው። የምታይበት መንገድ የምትደርስበትን ግብ፣ የምታገኘውን ነገር፣ የምታመጣውን ውጤት፣ የምታተርፈውን ትርፍ፣ የምታፈራውን ወዳጅ፣ ይወስነዋል። ዓለማ ያለው ሰው ዓለማውን ሳያሳካ መመለስ የለበትም። የተጀመረውን መጨረሻ ማድረስ ደግሞ ከሌሎች ተግባራት በበለጠ በትዳር ሕይወት ላይ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Discover more from Mahidere Tsibeb

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
Get started