
ዛሬ ቢቢሲ ባወጣው ሰበር ዜና ዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) የሚባለውና ስቴሮይድስ (Steroids) ከሚባለው ቤተሰብ የሚመደበው የመድኃኒት ዓይነት ኮሮና ላይ ከሚደረገው ጥናት ውስጥ የሞት መጠንን በመቀነስ አጥጋቢ ውጤት ማምጣቱን ዘግቧል ።
ዛሬ ስለተሰማው መልካም ዜና ብዙዎቻችን እንደሰማን እርግጠኛ ነኝ። ዜናው በአጭሩ የሚለው ዴክሳሜታዞን የሚባለው በአለም ዙሪያ በስፋት ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውለው መድሃኒት በኮቪድ ፅኑ ህመም ላይ ላሉ ታካሚዎች ቢሰጥ የሞት ቁጥር በ1/3ኛ እንደሚቀንስ አሳይቷል።
ጥናቱ በበርካታ ህሙማን የተደረገና ተቀነባይነቱ ከፍተኛ ስለሆነ እጅግ ግሩም ዜና ቢሆንም ጥቂት ማብራሪያዎች ግን ልብ ማለት ያሻል:-
- የጥናቱ ትኩረት የኮቪድ ሞትን መቀነስ በመሆኑ ያተኮረው የሞት አደጋ ያለባቸውን ፅኑ ሕሙማንን ነው። ጠቀሜታውም በተለይ ለእነዚህ ፅኑ ህሙማን እንጂ ለሁሉም የኮቪድ ህሙማን አይደለም። ቀላል ህመም ላላቸው ሰዎች አልተመከረም፣ እንዲሁም ለመከላከል ቢውል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይቻላል።
- ይሄም መድሃኒት ሆኑ ወንድሞቹ (steroids) ከሌሎች መድሃኒቶችም በሚልቅ መልኩ በርካታ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላሉ። የሞት አፋፍ ላይ ላሉ ህሙማን ከጉዳቱ ጥቅሙ ቢያመዝንም ለሌሎች ግን ጎጂ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ለብዙዎቹ ፅኑ ህሙማን ቢጠቅምም የተወሰኑትን ግን ጭራሽ አባብሶ ለሞት ሊያበቃ እንደሚችል እናስተውል::
እንዲሁም ከእነዚህ መድሃኒቶች መጥፎ የጎንዮሽ ጉዳት አንዱ የሰውነትን የመከላከያ ሃይል ማዳከም ስለሆነ ምናልባትም የህመሙ ጅማሬ ላይ ከተሰጠ ጭራሽ የቫይረሱን የመራባት አቅም አባብሶ ለአደጋ ሊዳርግ እንደሚችል መላ ምት አለ። - ይሄ መድሃኒት አገራችንን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በስፋት የሚገኝ መሆኑ የዜናው አስደሳች ጎኑ ነው። ሌላኛው ጠቀሜታ እንዳለው የተጠቆመው ሬምዴሲቪር የተባለው መድሃኒት እጅግ ውድና ለአገራችን የማይታሰብ ነበር።
- አብዛኞቹ የዜና አውታሮች ላይ ዜናው ሞቅሞቅ ተደርጎ ቢቀርብም “ተዓምራዊ ፈውስ “(miracle cure) እንዳልሆነ ልብ እንበል።
በጥናቱ እንደታየው ለምሳሌ
የእስትንፋስ እገዛ ካስፈለጋቸው ሰዎች በአማካይ ከመቶ ውሰጥ አርባዎቹ የሚሞቱ ሲሆን በአንፃሩ ይሄ መድሃኒት ከተሰጣቸው ውስጥ የሚሞቱት 28ቱ ናቸው። ከመቶ ፅኑ ህሙማን 12ቱ በዚህ የተነሳ ተረፉ ማለት ነው። ቀላል አይደለም፣ ተኣምራዊ ፈውስ ግን አይደለም።
የኦክስጅን እገዛ ካስፈለጋቸው ሰዎች ከመቶ 25ቱ የሚሞቱ ሲሆን፣ በዚህ መድሃኒት የሟቾች ቁጥር ወደ20 ይወርዳል። እዚህኛው ላይ ጠቀሜታው ዝቅ ያለ ነው።
ይሄ ጥራቱን የጠበቀ ምርምር እንደሆነ ቢነገረም እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ሌሎች መጠነሰፊ ምርምሮች በተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ሲያረጋግጡት ብቻ ነው። ነገርግን “ብልጥ ልጅ የሰሰጡትን ይዞ ያለቅሳል” ስለሆነ እስከዛው መልካም ዜና ነው።
Leave a comment