ተከታይሽ ሁሉ አድናቂሽ አይደለም

ተከታይሽ ሁሉ አድናቂሽ አይደለም፡፡ ያሞገሰሽ ሁሉ ያፈቀረሽ አይደለም፡፡ የሳቀልሽ ሁሉ ወዳጅሽ አይደለም፡፡ ትሁት ሁሉ መልካም ሰው አይደለም፡፡ አነጋገሩ የሚያምር ሁሉ አዋቂ አይደለም፡፡ የሰበከሽ ሁሉ ፃድቅ አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን የሳመ ሁሉ ክርስቲያን አይደለም፡፡ የሳቀ ሁሉ ደስተኛ አይደለም፡፡ ሴትነትሽን ሊያረክስ የሚፈልግ፣ ቀንበጥነትሽን ለመቀንጠስ የሚሽቀዳደም፣ ወጣትነትሽን ሊያኮላሽ ያሰፈሰፈም ከኋላሽ ይከተልሻል፡፡ የሚከተልሽን ሁሉ አትመኚ፡፡ አንዳንዱ ተከታይሽ ከዓላማሽ ሊያደናቅፍሽ፤ ከመንገድሽ ሊያስቀርሽ ጊዜና ቦታ እንዲገጥመው የሚከታተልሽ ሊሆን ይችላልና፡፡

በሆነ ባልሆነው ሊያሳስቅሽ የሚፈልግ ወንድን ጠርጥሪ፡፡ አሁን ይስቅልሻል፤ ኋላ ይስቅብሻል፤ በሌሎችም ያስቅብሻል፡፡ አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓቹም አሁን ያዝንልሻል፤ በኋላም ያሳዝንሻል ወይም ያስለቅስሻል፡፡ ወደድኩሽ ከሚልሽ ሰው ይልቅ ጠላሁሽ የሚልሽን ታውቂዋለሽ፡፡ አፍቃሪ ከባድ ነው አይታወቅም፤ ጠዪ ግን ቀላል ነው፤ ታውቂዋለሽ፡፡ አንዴ የጠላሽ ሰው ችግር አያመጣም፡፡ የወደደ እየመሰለ ልቡ ግን የሚጠላሽ አስብቶ አራጅ ነው፡፡ የአንዳንዱ ፍቅር ልክ እንደንጉስ ዳዊት ልጅ እንደአምኖን፤ ፍቅሩ የወረት ነው፡፡ የሚፈልገውን ካገኘ በኋላ ‹‹ከወደድኩሽ ውድ ይልቅ የጠላሁሽ ጥል በለጠ›› ብሎ አንቅሮ ይተፋሻል፡፡

ዓለምን መከተል ሴትን መከተል ነው፡፡ ዓለም አምሮት ነው፤ አምሮቱም ከሴት በላይ አይደለም፡፡ ‹‹ዓለም የዓይን አምሮት፤ የስጋ ምኞት ነው›› እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ተወደደም ተጠላ የዓይን አምሮቱም ሆነ የስጋ ምኞቱ ዋና ማረፊያ ሴት ነች፡፡ ወንዶች አመኑም አላመኑም ሴት የወንድ መሪ ናት፡፡ ወንድ ደግሞ የሴት ተከታይ ነው፡፡ ቅዱሱ መፅሐፍ ‹‹የሴት ራስ ወንድ፤ የወንድ ራስ ክርስቶስ ነው›› ቢልም የወንዶች ራስ ግን ሴት ሆናለች፡፡ ዓለምን የምታሽከረክረው ሴት ነች፡፡ የሴት ስልጣን በአካል አይታይም፡፡ በመንፈስ ግን የወንድን ስሜትና አዕምሮ ተቆጣጥሮ እየገዛ ነው፡፡ ለሴት ያልተንበረከከ ወንድ የለም፡፡ ሴትነት ፊት ነው፤ ወንድነት ኋላ ነው፡፡ ሴትነት ኋላ ይሆን ዘንድ ያለቦታቸው ፊት የቆሙ ብዙ ወንዶች አሉ፡፡ ሴትነትን አርክሰው መሪነትን ለወንድ አሳልፈው ሰጥተው ከወንድ ኋላ የቆሙም ብዙ ገልቱ ሴቶች አሉ፡፡ ሁለቱም ያለቦታቸው ቆመዋል፡፡

አንቺ ግን ክብርሽን ጠብቂ፡፡ ሴትነት መቅደስ ነው፤ መቅደስሽን በውሾች አታስደፍሪ፡፡ ፊት ሁኚ! ኋላ አትቅሪ! በአስተሳሰብ ቅደሚ! በዕውቀት ለምልሚ፤ በብልህነት አትበለጪ፡፡ ፍቅርሽን የምታጋሪውን፤ ክብርሽን የምታካፍዪውን ወንድ ለይተሸ እወቂ፡፡ የጠቀሰሽና ያሽኮረመመሽ ሁሉ የወደደሽ አይደለምና ወረት የሌለበትን ታማኝ ወንድ ለዪ፡፡ ገንዘብና ዝና አይማርክሽ! በወርቅና በብልጭልጭ ነገር አንቺነትሽን አታርክሺ፡፡ ገዢሽ ፍቅር ይሁን! ፍቅርሽም አንድ ይሁን!

                 ✧━━━━━🖊━━━━━✧‌‌

Discover more from Mahidere Tsibeb

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
Get started